top of page

የደብሩ አስተዳደር መልዕክት


ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደኅነተ ዓለም ወደዚህ ምድር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ለሰው ልጅ ድኅነተ ነፍስ የሆነውን ትምህርት እያስተማረ ለምግበ ሥጋቸውም የሚሆነውን በተዓምራቱ ጥቂቱን እያበረከተ በሰው ያለውን ደዌ ሥጋ እየፈወሰ በጎና አርአያነት ያለውን ሥራ ሁሉ ፈጽሞአል።(ማቴ 15: 29-39) በዘመነ ስብከቱም ሲያስተምር በምሳሌ ነበር (ማቴ13፡ 34) ከምሳሌዎቹ ወደ ተነሳንበት ርዕስ የሚወስደንን እንመልከት አንድ ባለጸጋ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ በአሰበ ጊዜ አገልጋዮቹን ጠርቶ ወጥተው ወርደው አትርፈውበት እንዲጠብቁት ለእያንዳንዳቸው እንደየአቅማቸው ገንዘብ ሰጣቸው። የገንዘቡም መጠን በመክሊት ሆኖ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት መክሊት ለአንዱም አንድ መክሊት ሰጠና ሄደ። ከእነርሱም ሁለቱ ጌታቸው እንዳዘዛቸው ሁሉ ውለው ሳያድሩ ትርፋማ ለመሆን መውጣት መውረዱን ተያያዙትና አምስት መክሊት የተቀበለው ሌላ አምስት መክሊት አትርፎበት ዐሥር አደረገ ባለ ሁለት መክሊት የተቀበለውም ሁለት አትርፎበት አራት አደረገ። አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ጌታው እንዳዘዘው ወጥቶ ወርዶ ሳያተርፍበት የተሰጠውን መክሊት ምድር ቆፍሮ ቀበረው። ከብዙ ዘመን በኋላ የባለመክሊቱ ጌታ መጣና እያንዳንዳቸውን ጠርቶ ገንዘቡን ከነትርፉ እንዲያስረክቡት በጠየቃቸው ጊዜ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀረበና ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እንዳዘዝከኝ ወጥቼ ወርጄ ከአተረፍኩት አምስት መክሊት ጋር ዐሥር አድርጌአለሁና እነሆ መክሊትህን ከእነትርፉ ተቀበለኝ አለው። ባለሁለት መክሊቱም እንደዚሁ ቀርቦ ወጥቶ ወርዶ ካተረፈበት ሁለት መክሊት ጋር አራት አድርጎ አስረከበ። ጌታቸውም በእነዚህ ታማኝ አገልጋዮች እጅግ ተደሰተ እንዲህም አላቸው እናንተ ታማኝ አገልጋዮች በጥቂቱ ታምናችኋዋልና በብዙ እሾማችኋለሁ ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ አላቸው። አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ትርፋማ ባለመሆኑ በፍርሀት እየተንቀጠቀጠ ወደ ጌታው ቀርቦ እንዲህ አለ አቤቱ ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንክበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ ስለዚህ ፈርቼ መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀብሬ ነበር እና እነሆ ተቀበለኝ አለ። ጌታውም ተቆጥቶ በኃይለ ቃል እንዲህ ሲል ተናገረው ‘’አንተ ክፉና ሃኬተኛ /ሰነፍ/ አገልጋይ ካልዘራሁበትን እንደማጭድና ካልበተንኩበትን የምሰበስብ መሆኔን ካወቅህ ዘንድ እንዳዘዝኩህ ባለመፈጸምህ ወደ ዘላለም ጨለማና ስቃይ ሂድ በማለት ጭፍሮቹን ጠርቶ በእጁ ያለውን መክሊት ተቀብለውት አምስት መክሊት ላተረፈው ታማኝ አገልጋይ እንዲሰጡትና እሱን ግን እጅና እግሩን አስረው ጨለማና ስቃይ ወደ አለበት እንዲወስዱት አዘዘ።(ማቴ 25:29)

1 view0 comments
bottom of page